እውን “የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እና የመሐመድ አምላክ” አንድ ናቸውን?

እውን “የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እና የመሐመድ አምላክ”

አንድ ናቸውን?[i]

በተካልኝ ዱጉማ

(Duguma@gmail.com)

ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ የዓለም ሁሉ ትኩረት የሆነው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ነው። በዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ይህ ኃይማኖት ከፍተኛ ተጽእኖ ማምጣቱ ሀገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው እውነት ነው። ለዚህም ይመስላል በአሁን ሰዓት ሙስልሞችን በወንጌል የመድረስ ራዕይን የሰነቁ ሰዎችን በብዛት መመልከት የጀመርነው። ይህ ደግሞ እሰየው የሚያስብል ነው። ምንም እንኳ አንዳንድ የሚያስፈሩኝ ነገሮች ቢኖሩትም። ድሮ ድሮ የሙስልሞች ቁጥር እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ የምንመለከታቸው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። ነገር ግን አሁን ቁጥራቸው በዝቶ እልፍ አላፍ ሆነዋል። እንዲያውም በአንድ አንድ ቦታዎች በቁጥር በልጠው ይታያሉ። ኢትዮጵያም የክርስቲያኖች ደሴት የመባሏ ነገር ተረት ልሆን ትንሽ የቀረው ይመስላለ። ዛሬ በዚህ ጽሑፍ የሙስልሞችን የቁጥር እድገት ወይም በሀገራችን እና በዓለማችን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያስከተሉትን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽእኖ ለመዳሰስ ሳይሆን እንደ ቀልድ ብዙ ግዜ ስለው የነበረ ነገር ግን ድንገት አንድ ቀን በደንብ እንዳጤነው እና እንዳስብበት ስለተገደድኩበት አንድ ነገር ላካፍልችሁ ስለፈለግኩ ነው። እንደ ቀልድ ብዙ ግዜ ሰዎች “የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እና የመሐመድ አምላክ ይባረክ” ሲሉ አድምጫለሁ የነገሩን ምንነት ጠንቅቄ ባላውቅም በቀልዳቸውም ተሳትፌ የማውቅ ይመስለኛል። ይህ ቀልድ አዘል ንግግር መሰረት ያደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው የኢየሱስ ክርስቶስ አባት (እግዚአብሔር አብ) እና በቁራን የተገለጠው የመሐመድ አምላክ (አላህ) አንድ ናቸው በሚል እሳቤ ላይ ነው። ይህን እንደ ቀልድ ስመለከተው የነበረውን ሀሳብ በጥንቃቄ እንዳስብበት ያደረገኝ በክፍል ውስጥ የገጠመኝ ነገር ነው። cultural Anthropology አስተማሪያችን ትምህርቱን ይበልጥ በየእለት ህይወታችን ተግባራዊ እንዲሆን በመፈለግ ይመስላል ተጋባዥ አስተማሪዎችን ይጋብዛል። እኛም ደስ ብሎን ክፍለ ግዜውን እንከታተላለን። የዚያ እለት ተጋባዥ አስተማሪው በአብያተ ክርስቲያን ሕበረት የሙስልም ሚንስትሪ አስተባባር በመሆን የሚያገለግል በመሆኑ እንዴት ሙስልሞችን በወንጌል መድረስ እንደሚቻል ከዚህ በፊት አስቤበት የማላውቀውን የአውዳዊነትን መንገድ ገለጸ። ያነሳቸው ሀሳቦች ከተለመደው መንገድ የወጡ በመሆናቸው (ነገሩ የሚያስደነግጥ)፤ እናም እሰየው የሚያስብል (ለዘመናት የተዘነጉት ሙስልሞችን በወንጌል ለመድረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ በመሆኑ) እንዲሁም በአሁን ሰዓት የዓለማችን እና የሀገራችን ትልቅ ስጋት እየሆነ ለመጣውን የእስልምና ¹ይማኖት እድገት የበኩሉን መፊቴሔ ለመስጠት የተነሳ በመሆኑ የተደባለቀ ስሜት ፈጠረብኝ። ነገር ግን ያነሳቸው ሃሳቦች በጣም ስላስፈሩኝ በጥንቃቄ ለማሰብ ተገደድኩኝ። ነገሩ በዚይህ አላበቃ ብሎ ከጥቅት ጊዜ በኃላም በአብያተ ክርስቲያን ደረጃ አንድ የእስልምናን ባሕል ማዕከል ያደረገ “ባሕል እና ቋንቋ ዘለቅ” የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ልተረጎም መሆኑን የወሬ ወሬ ሰማሁኝ። መስማት ብቻም አይደል በቤተ ክርሰቲያኔ አማካኝነት በዚይሁ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይትን ልካፈል በቅቻለሁ።

በዚህ ጽሑፌም የምዳስሰው በአሁን ሰዓት ለሙስልሞች ወንጌልን ለመመስከር ውጤታማ የሆነው አውዳዊነት መንገድ የትኛው ነው? የሚለውን ሳይሆን የትኛውም በእስልምና ዙርያ የሚደረግ ማንኛውም አውዳዊነት ስለሚዳስሳቸው ወይም በጥንቃቄ ሊያካትታቸው ስለሚገቡ ሀሳቦች  እና ቃላት ምንነት ነው። በመጀመሪያ አላህ የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተገለጠው አምላክ መጠቀም በቃሉን ሥርወ ግንድ ጥናት ድጋፍን ቢያገኝም፤ በዘመናችን በሰዎች አዕምሮዎ ቃሉ ያለው ትርጓሜ ግን አቻ ትርጓሜ አድርገን መውሰድ እንደማይገባን የሚያሳይ መሆኑን አሳያለሁ። ሁለተኛ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው አምላክ እና በቁራን የተገለጠው አምላክ አንድ አለመሆናቸውን አስረዳለሁ። በመጨረሻ በርዕሰ አንቀጹ ላይ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ በሁለት መንገድ በመግለጽ አጠናቅቃለሁ።

“አላህ የሚለው ቃል ከመሐመድ መምጣት በፊት በአረብ ምድር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አማልክቶቻቸውን ለመጥራት ይጠቀሙበት እንደ ነበር የሚያሳይ ታርካዊ፣ ስነ-ጽሑፋዊ እና ስነ-ቅርሳዊ ማስረጃዎች አሉ።”[ii] እስልምና በአረብ ውስጥ ከመጀመሩ በፊት “በአረብ ውስጥ ጸሐይ እንደ ሴት አማልክት ጨረቃ ደግሞ እንደ ወንድ አምላክ ይታዩ ነበር። ወንድ አምላክ የሆነው ጨረቃ የተለያዩ መጠርያዎች ይጠራል። አላህም በአረብ ምድር ከነበሩት አማልክት መካከል አንዱ እና ከሁሉም በላይ ነበር። . . . መሐመድ በኖረበት ዘመን የአንድ አላህ ብቻ አምላክነት በአረብ ውስጥ እየተስፋፋ መጥቶ ነበር። የዚህም ምክንያት አረቦች ከክርስቲያኖች እና ከአይሁዶች ጋር ባላቸው ግንኙነት ባደረባቸው ተጽእኖ ወይም በኢ-አማንያን ጎሳዎች መካከል የራሳቸውን የጎሳ አምላክ አላህ ብሎ በመጥራት በተነሳው አለመስማማት ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳ አላህ ከሁሉ በላይ እና ፈጣሪ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረውም በኢ-አማንያን ዘንድ ግን ይህ የተዘነጋ እውነት ነበር።”[iii] እንዲሁም “ከእስልምና በፊት በአረብ ውስጥ በሚኖሩ ኢ-አማንያን ዘንድ አላህ ብቸኛው መለኮት ሳይሆን ረዳቶች፣ አጋሮች፣ ወንድ እና ሴት ልጆች አሉት። ነገር ግን ይህንን አመለካከት (አላህ ረዳቶች፣ ሴት እና ወንድ ልጆች እንዲሁም አጋሮች አሉት የሚለውን) የእስልምና ኃይማኖት በጣም ይቃወመዋል።”[iv] ከእስልምና በአረብ ሀገራት ውስጥ ከመወለዱ በፊት “አላህ” የሚለውን ቃል ስንመለከት አሁን ቁራን ከሚሰጠው ተርጉም ይለያል። “ሙስልሞች (ከመሐመድ መምጣት በፊት እንደነበሩት በአረብ ውስጥ ይኖሩ እንደ ነበሩት ሰዎች ሳይሆን)[v] አላህ የሚለውን ስም ለብቸኛው እና እውነተኛው አምላክ እንጂ ለሌሎች አማለክት አይጠቀሙበትም::”[vi] ነገር ግን “ከእስልምና መምጣት በፊት በመካ ውስጥ አላህ የሚለው ስም አንድ ፈጣሪ እና ከሁሉ በላይ የሆነን አምላክን ያመለክት ነበር”[vii]። ይህ በመካ ውስጥ አንድ አላህ ብቻ ይመለክ ነበር ወደ ሚል መደምደሚያ ግን አያደርሰንም። ለዚህ ምክንያት የሚሆነኝ በዘመናት መካከል የተገለጡ የተለያዩ አይነት የአንድ አምላክ አምልኮት ደረጃዎች አሉ። የእነዚህ ደረጃዎች እድገት ፍጹም ወደ ሆነው ወደ ፍልስፍናዊ እንድ አምላክ አምለኮ ደረጃ ማደግ ነው። እነርሱም፦

ፍልስናዊ አንድ አምላክ አምልኮት (ይህ አይነቱ የአንድ አምላክ አምልኮት አንድ አምላክ ብቻ በምድር ላይ ይገኛል የሚል ፍጹማዊ ደረጃ ነው)፣ ሁለተኛው ሄኖቴይዝም ይባላል (ይህ ሌሎች አማልከት መኖራቸውን ሳይክድ ከሁሉ በፊት ግን እነርሱ የሚያመልኩት አንዱ አምላክ ከሁሉ በላይ እንደሆነ የሚያምኑ ናቸው)፣ ሶስተኛው ሞኖላትር የሚባለው የአንድ አምላክ አምልኮ ሲሆን (ይኸውም ሌሎች አማልክት ይኑሩም አይኑሩም ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አንዱ አምላክን ብቻ ለማምለክ የወሰኑ ናቸው)። የመጨረሻው ተግባራዊ የአንድ አምላክ አምልኮ (ይህ ሌሎች አማልክት መኖራቸውን ሳይክድ አብዛኛው ¹ይማኖታዊ እና የአምልኮ ተግባሮች የሚከናወኑት አንዱን አምላክ ብቻ ማዕከላዊ ባደረገ መልኩ ሲሆን ነው)። [viii]

“ከእስልምና በፊት ብዙ አረቦች በአንድ ከሁሉ በላይ በሆነ፣ ሁሉን በሚችል እና የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ በሆነ አምላክ ያምኑ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ተጨማሪ ከዚህ አምላክ በሚያንሱ ትንንሽ አምላኮችም ያምኑ ነበር።”[ix] ይህ ሁሉን የሚችል እና የሁሉ ፈጣሪ አምላክ፣ ረዳቶች የነበሩት መሆኑን ያምኑ እነደ ነበር በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ሰዎች ይናገራሉ። “ከእስልምና በፊት የነበሩት አረቦች አላህ እነርሱ ትንንሽ አማልክት የሚሏቸው ረዳቶች እና አጋዦች  ነበሩት።”[x] ይህ እንግዲህ አላህ የሚለው ቃል ከእስልምና መወለድ በፊት ሌሎች አማልክት መኖራቸውን ሳይቃወም አንድ ከሁሉ በላይ የሆነ መለኮትን የሚያመለክት ቃል እንደሆነ እንመለከታለን።

እንዲሁም አላህ የሚለው ቃል ሥርወ ግንድ የጥንት የሴም ነገዶች ቋንቋ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። “አላህ የሚለው ቃል ምንጩ መለኮትን ከሚያሳይ ከጥንት የሴም ነገዶች ቋንቋ ነው። ከነዓናዊያን መለኮትን ‘ኤል’ ሲሉ ሜሴፖታሜያዊያን ‘ኢሉ’ ይላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ የመለኮት ስያሜ ‘ኤሎሄም’ ነው።”[xi] እኔ በዚህ ስፍራ ላይ ማሳየት የፈለግኩት አላህ የሚለው ስም ከእስልምና ኃይማኖት መወለድ በፊት አማልክትን ለማመልከት በአረብ ውስጥ ይጠቀሙበት የነበረ መሆኑን እና አላህ የሚለው ቃል ሥርወ ግንድ በሴም ነገዶች ቋንቋ ውስጥ መሐመድ ከመምጣቱ በፊት መለኮትን ለማመልከት ይጠቀሙበት የነበረ መሆኑን  ነው። በዚህ ምክንያት አላህ የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተገለጠው አምላክ መጠቀም በራሱ ምንም ችግር ያለው አይመስል። ነገር ግን የቃላት ትርጓሜ በሥረወ ግንድ ፊች ብቻ ላይ ነው ማለት ግን አይቻልም።

ሌላኛው በጥንቃቄ ልንመለከተው የሚገባው ነገር አላህ በሚለው የአረብኛ የመለኮት መጠርያና ኤሎሄም በሚለው የዕብራይስጥ የመለኮት መጠርያ መካከል ያለውን ዝምንድናን ነው። አንዳንድ ሙስልሞች ይህንን መመሳሰል አይቀበሉትም። ምክንያቱም ኤሎሄም የተጽዎ ስም ሳይሆን ለአማልክት የሚሰጥ አጠቃላይ ስም (የወል ስም) ነው ይላሉ።[xii] ኤሎሄም ሁሉን ቻይ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን እግዚአብሔር የተጽዎ ስም ብቻ ሳይሆን ለጣኦታት አማልክትም ስያሜ ሆኖ እናገኘዋለን። (ዘፍ 1፡1፣ መዝ 69፡5) ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች አላህ የሚለው ስም በተጽዎ ስምነት እንጂ እንደ ኤሎሄም የአማልክት መጠርያነት (የወል ስም) አይደለም ይላሉ[xiii]። ስለዚህ ሁለቱ ስያሜዎች ተለዋዋጭ እና ተስተካካይ አይደሉም በማለት ይከራከራሉ። “አላህ የሚለው ስም በጣም ጠቃሚ የሆነ የአምላክ ስም ነው። ከኤሎሄም ይልቅ ያሕዌ ከሚለው የእግዚአብሔር ስም ጋር ይተካከላል ብለው አንዳንድ ሙስልም ሊቃውንት ያምናሉ። “አላህ” ለአማልክት የተሰጠ የወል ስም ሳይሆን የተጽዎ ስም ነው። በቁራን የተገለጠው አምላክ መጠሪያ ስሙ ነው ይላሉ። ሙስሊሞች አላህ የሚለው ስም ለአማልክት የተሰጠ የወል ስም ነው የሚለውን አስተምህሮ ይህ ቃል ልዩ እና ከሌላ ቃል በውርስ ሊመጣ አይችልም በማለት ይቃወሙታል።”[xiv] ነገር ግን Timothy C. Tennent የተባሉ ምሁር አላህ ከኤሎሄም ጋር የሚያመሳስለውን አራት ዋና የሚባሉ ነጥቦችን አስቀምጠዋል “

  1. 1. ግልጽ የሆነ የቃሉ ሥርወ ግንድ አላህ በሚለው በአረብኛ ቃል እና ኤሎሄም በሚለው የዕብራይስጥ ቃል መካከል መመሳሰል መኖሩን ያሳያል።
  2. 2. ከእስልምና በፊት በአረብ አከባቢ በሚኖሩ ሰዎች አላህ የሚለውን ቃል አንድ “አምላክ አምላኪ”[xv] በሆነ ሰዎች መካከል ለአንድ ሉዓላዊ ለሆነ አምላክ ይጠቀሙበት እንደ ነበር ብዙ ታሪካዊ እና ስነ- ቅርሳዊ ማስረጃዎች አሉ።
  3. 3. በአይሁዳዊያንም ይሁን በክርስቲያኖች መጽሐፍት ትርጉም ውስጥ “አላህ” ከጥንት  ጀምሮ እስዛሬ ድረስ በእግዚአብሔር ስምነት ሲተረጎም ቆይቷል።
  4. 4. “አላህ” የሚለው ስም ሰፋ ያለ ትርጉም ያለውን የአምላክ ስምን ለመተርጎም ተጠቅመውበታል እንጂ ግላዊ፣ ለሙሴ የተገለጠውን የቃል ኪዳን ስም የሆነውን ያህዌን ለመተርጎም አልተጠቀሙበትም። አይሁዳዊያን እኛ አምላክ የሚለውን ቃል ለቃል ኪዳኑ አምላክ እና ለሀሰተኛ አማልክት እንደምንጠቀምበት ሁሉ እነርሱም ተጠቅመውበታል። ነገር ግን ሙስሊሞች (ከመሃመድ መምጣት በፊት እንደነበሩት በአረብ ውስጥ ይኖሩ እንደ ነበሩት ሰዎች ሳይሆን)[xvi] አላህ የሚለውን ስም ለብቸኛው እና እውነተኛው አምላክ እንጂ ለሌሎች አማልክት አይጠቀሙበትም።”[xvii]

“ኤሎሄም የሚለው ቃል  “ኃያል” የሚል ትርጓሜ አለው።  ይህ ቃል በብዙ ቁጥር በመገለጽ አክብሮትን በሌላ ግዜ ደግሞ “ሁሉን ቻይነትን” እንደሚያሳይ ማሰቡ ትክክል ነው። ይህ አላህ የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተገለጠው አምላክ መጠሪያነት (በተዋጾ ስምነት) ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ መለኮትን ለሚያመለክቱ ሁሉ ስም (በወል ስምነት) ውሏል። (መዝሙር 82፡1፣ 1ሳሙኤል 28፡13)”[xviii] እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው በአላህ እና ኤሎሄም በሚለው የአምላክ ስም መካከል ትልቅ መቀራረብ መኖሩን ያሳያሉ። ሁለቱም ስሞች የሚያገለግሉት እንደ የተዋጾ ስም (Personal name) ሳይሆን እንደ በጠቅላላ መለኮታዊ ባሕይር አላቸው ተብሎ ለሚታመን አማልክት ስምነት፣ የወል ሰምነት (Generic name) ነው። ሁለቱም የሚያሳዩት አንድ ሁሉን ቻይ፤ ኃያል አምላክን እንጂ እንደ ያሕዌ የቃል ኪዳን አምላክ የሆነውን ለሙሴ የተገለጠውን የአንድ አምላክ መጠሪያ ስምነት አይደለም። ነገር ግን ቃለት ትርጓሜ ምንጭ የቃላቱ ሥረወ ግንድ ብቻ መሆን የለበትም። ማህበረሰቡ እነዚይህን ቃላት እንዴት ይጠቀምባቸዋል፣ እነዚይህ ቃላት በሰው በማህበረሰቡ ውስጥ ከምን ጋር የተቆራኙ ናቸው ብሎ መሳብ አስፈላጊ ይሆናል። ለምሳሌ በጎጀም ወይም በጎንደር ያለ አንድ ሰው “በመኽና ላይ ስቀለኝ” ስል የዚይህ ቃል ትርጉም በመክናው ውሰደኝ፣ አሳፍረኝ ማለት ሲሆን፤ ለመሃል ሀገሩ ሰው ግን ይህ ሀረግ ትርጓሜው በመክና ላይ እነቀኝ፣ አንጠልጥለኝ የሚል ይሆናል። ስለዚይህ ቃላት በተጠቀሱበት አውድ የተለያዩ ትርጓሜዎች ይኖሯቸዋል። አላህ የሚለው ቃል ሥረወ ግንዱ አምላክ የሚል ትርጓሜ ቢኖረውም እንዲሆን ክርስቲያን አረቦችም ይህንን ስም ለመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ መጠርያነት ብጠቀሙበትም ይህ ቃል ወደ ኢትዮጵያ ክርስቶያኖች ወይም ሙስልሞች ስንመጣ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገለጠውን አምላክን አያመለክትም። ሙስልሞችም ይሁን ክርስቲያኖች አላህ የሚለውን ስሰሙ ወደ አእምሮአቸው የሚመጠው የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ሳይሆን የቁራኑ አምላክ ነው። ምክንያቱም ይህ ቃል የተለያየ አምላክ እንደሚያመልክ ያስባሉና። ስለዚይህ “አላህ” የሚለው ቃል በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ተብሎ ለተተረጎሞት ቃላት አቻ ትርጓሜ አይደለም።

ወደ ሁለተኛው ሀሳብ እናምራ። በመጸሐፍ ቅዱስ የተገለጠው እግዚአብሔር (ተለዋጭ ስሙ አላህ) በቁራን ከተገለጠው ጋር አንድ ናቸውን? ወይም በሌላ አባባል በዋናነት የዚህ ጥያቄ መሠረት ሙስልሞች የሚያመልኩት አምላክ እና ክርስቲያኖች እና አይሁዶች የሚያመልኩት አምላክ አንድ ነውን? የሚል ነው። በዓለማችን ላይ ሶስት አንድ አምላክን አምላኪ ኃይማኖቶች አሉ። እነርሱም ክርስትና፣ እስልምና እና የአይሁዳዊያን ኃይማኖቶች ናቸው። እነዚህ ኃይማኖቶች በዓለማችን ላይ አንድ ሁሉን የሚገዛ እና የሁሉ ፈጣሪ የሆነ አምላክ እንዳለ ያምናሉ። ጥያቄው ሁሉም አንድ አምላክ እንዳለ የሚያምኑ ከሆነ አንዱ አንዱን ልክ አይደለህም ማለት ይችላልን?  የሚል ነው። ስለዚህም አንዳንድ ሰዎች “ክርስትያኖችም ይሁኑ ሙስልሞች ስለ እርሱ (ሰለ ፈጣሪያቸው) ሲያወሩ፣ በምንም ስም ይጥሩት የሚያወሩት ስለ አንዱ አምላክ ነው ይላሉ”[xix]። Mideast & N. Africa Encyclopedia እንዲህ ይላል “ማስተዋል የሚገባን ነገር እንደ ሙስልሞች አስተምህሮ አላህ የነብዩ መሃመድ አምላክ ብቻ አይደለም ነገር ግን የሙሴ እና የኢየሱስም አምላክ ጭምር እንጂ። ስለዚህ የአይሁዳዊያን እና የክርስቲያኖች ቅዱሳት መጽሐፍት ከሚያመለክቱት መለኮት ጋር አንድ ነው”[xx]። ግን ይህ ዓረፍተ ነገር ልክ ነውን? በጭራሽ! የሁለቱም የኃይማኖታቸው ወይም የእምነታቸው መሠረት በሃሳባዊ ወይም የፍልስፍና ቀመር ቢሆን ኖሮ አንድ ሁሉን ፈጣሪ፣ ከሁሉ በላይ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ አለ በማለታቸው የሚያመልኩት አምላክ አንድ ነው ባልንም ነበር። ነገር ግን ክርስቲያኖችም ይሁኑ ሙስልሞች እንዲሁ ተጨባጭ ያለሆነ ምናባዊ የሃሳብ ቀመር የሆነ አምላክን አያመልኩም። ነገር ግን ሁለቱም ይህ አምላክ እራሱን ገለጠበት ብለው የሚያምኑበት የእርሱን ማንነት የሚገልጽ መጽሐፍት አሏቸው። ስለዚህ ጥያቄው በቁራን ላይ የተገለጠው “አምላክ” እና በመጸሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው አምላክ አንድ ነው ወይ? የሚል ይሆናል።

እርግጥ ነው በመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ እና በቁራኑ “አምላክ” መካከል መመሳሰል መኖሩን መካድ አይቻልም። ነገር ግን ሁለቱ አንድ ናቸውን? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ግን አንድ አይደሉም ነው። እስልምናን እና ክርስትናን አንድ የሚያደረጋቸው ሁለቱም “በአንድ አምላክ”[xxi] ማመናቸው ነው ይባላል። ነገር ግን ስለዚህ አምላክ ባህርያት እና ድርጊት ሲናገሩ የመመሳሰል እና የመለያየት ነገርን ማስተዋል ይቻላል። ስለዚህ ነገር ቁራን እንዲህ ይላል “እኛ ለእኛ በተገለጠው እና ለእናንተ በተገለጠው እናምናለን። የእኛ እና የእናንተ አምላክ አንድ ነው”[xxii]። (ሱራ 29፡46) ይላል። ይህ ጥቅስ ሙስሊሞች የሚያመልኩት አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጠው አምላክ ጋር አንድ እንደሆነ እንደሚያምኑ የሚያሳይ ይመስላል። ነገር ግን በክርስቲያኖች መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ከቁራን ሀሳቦች ጋር በአንድ አንድ ቦታዎች የማይመሳሰሉበትን ምክንያት እንዲህ ይገልጹታል “የክርስትና ወይም የአይሁዳዊያን መጽሐፍት ሀሳብ ከቁራን ሀሳብ በሚቃረንበት ቦታ ሁሉ ይህ ሆን ተብሎ ወይም መጽሐፍቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ስህተት በኢ-እስላማዊ መጽሐፍት ውስጥ መኖሩን ሙስሊሞች ያምናሉ”[xxiii]። ስለዚህ ሙሲልሞች ምንም እንኳ አንድ  አምላክ እንዳለን ቢያስቡም ትክክለኛው አምላክ በእነርሱ ቁራን የተገለጠው እንጂ በእኛ፣ አሁን በእጃችን ባለው መጽሐፍ ላይ የተገለጠው አምላክ እንዳልሆነ ያምናሉ ማለት ነው። ስለዚይህ ክርስቲያኖች እና ሙስልሞች የሚያመልኩት አምላክ አንድ አይደለም ማለት ነው። ዛሬ በየትኛው መጽሐፍ ትክክለኛው አምላክ እንደተገለጠ በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት አልሞክርም ነገር ግን የእኔ ነጥብ የሆነው ሁለቱ መጽሐፍት የሚያሳዩት “አምላክ” ልዩነት ያለው መሆኑን ነው።

ስለዚህ በርዕሰ አንቀጹ ለተጠየቀው ጥየቄ ምላሽ እንስጥ። እውን “የኢየሱስ አባት እና የመሐመድ አምላክ” አንድ ናቸውን? ለሚለው ጥያቄ የእኔ መልስ አይደሉም እና ናቸው ይሆናል። አይደሉም የምልበት ምክንያት ሁለቱም ኃይማኖቶች አምላካቸውን የማወቅያ መንገዳቸው የተገለጠው በመጽሐፍቶቻቸው እስከ ሆነ ድረስ፤ በእነዚህ መጽሐፍት የተገለጠው አምላክ ምንም እንኳ መመሳሰል ቢኖረውም ልዩነት ስላለው አንድ አይደሉም ልል ተገድጃለሁ። ሁለት ምሳሌዎች ልስጥ። ሁለቱም ኃይማኖቶች አምላካቸው ሁሉን ቻይ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ሁሉን ቻይነቱን ሁለቱም የሚገልጹበት መንገድ ይለያያል። የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ኃያልነቱ በጥንካሬው ብቻ ሳይሆን በድካም ውስጥም እንደሚገልጥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንመለከታለን።  ለምሳሌ ሐዋሪያው ጳውሎስ እግዚአብሔር እንዴት ኃይላት እና ስልጣናትን እንዳሸነፈ ሲገልጥ እንዲህ ነው ያለው “እርሱ ያንን ይከሰንና ይቃወመን የነበረውን በሕግ ያለውን የዕዳ ጽሑፍ ደመሰሰው፤ በመስቀል ላይ ቸንክሮም ከእኛ አስወገደው። ኀይሎችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነሥቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው።” (ቆላስያስ 2፡14-15) ይህ እንግዲህ የእግዚአብሔር ኃያልነት በድካም የተገለጠበት የመስቀሉ ሥራ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ኃያልነቱን ማንም የማይቋቋመውን ኃይሉን በማሳየት ብቻ ሳይሆን የተገለጠው ሰዎችን ከ¹ጢአት እስራት ለማስለቀቅ እና የደንነት መንገድ ለማዘጋጀት ሞታቸውን በመስቀል ላይ ሞቶ፣ እንደ ሰው የሰውን ድካም ደክሞ፣ መከራን እና ስቃይን ተቀብሏል። ይህንን ዓይነት አመለካከት ግን የእስልምና እምነት እንደማይቀበለው በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ሰዎች እንዲህ በማለት ይናገራሉ። “የዚህን ዓይነት የመለኮት ¹ያልነትን [መለኮት መከራን እና ስቃይን ይቀበላል] የሚል አመለካከት ግልጽ በሆነው በባህላዊው የእስልምና አስተምህሮ ውስጥ የሌለ እና ምክንያታዊነት የሚጎለው ነው”[xxiv] ይላሉ።ይህ አመለካከት ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው አምላክ መለያ ባሕርይው በመሆኑ ሁለቱን ልዩ ያደርጋቸዋል። ሌላኛው ለምሳሌ፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ከቁራኑ “አምላክ” የሚለየው ምሳሌ የክርስቲያኖች የማንነት መለያ እና የደንነታችን መሠረት የሆነው የስላሴ፤ የኢየሱስ አምላክነት፣ የትስብእት፣ የመስቀሉ የማዳን ሀይል እና የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የመነሳቱ አስተምህሮዎች ናቸው። ዛሬ በዚህ ጽሑፍ እነዚህን አስተምህሮዎች በጥልቀት ለመዳሰስ ሳይሆን ቁራን እነዚሀ ከላይ የዘረዘርኳቸውን አስተምህሮዎች ስለማያስተምር ሁለቱ መጽሐፍት በሚገልጡት አምላክ መካከል ልዩነት መኖሩን ለማሳየት ነው። ይህንን ያስረግጥልኝ ዘንድ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጠው አምላክ እና ቁራኑ በሚገልጠው አምላክ መካከል ያለውን ልዩነት እና መመሳሰል ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ አንድ የእስልምና ምሁር የተናገሩትን ልጥቀስ “ስለ አሀዱ ስሉስ እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ያላችሁን አስተምህሮ ብትተዉ እኔ እና እናንተ የምናመልከው አንድ አምላክ ነው።”[xxv] ብለዋል። ጥያቄው ይህ በእርግጥ ነውን? የሚል ነው። በጭራሽ!  እነዚህ ተዉ፤ አትንኳቸው የተባሉትን አንኳር የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እና የክርስትና እምነት መሰረቶች እና መለያ እውነቶችን ብንተዋቸው ምን ይቀርልናል? ክርስቲና ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች ውጭ ከንቱ ዲስኩር  ነው። እነዚህ የእምነታችን መሠረት እና የተስፋችን ምንጮች ናቸው።

በመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ እና በቁራኑ “አምላክ” መካከል መመሳሰል ሊኖር ይችላል ነገር ግን በፍጹም አንድ ናቸው ማለት ግን አይደለም። ስለዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ አባት በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው አምላክ ከሆነና የመሐመድ አምላክ በቁራን የተገለጠው “አምላክ” ከሆነ ሁለቱ አንድ አይደሉም። የሚያመሳስላቸው በሕርያት አሏቸው እንጂ።

አንድ ናቸው ያልኩበት ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው አምላክ የኢየሱስ አባት ለመሆኑ እንዲሁም የዓለማት ፈጣሪ እና አስተዳዳሪ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ መሐመድ ከብዙ ዘመናት በፊት የኖረ ሰው በመሆኑ ምክንያት ያ የኢየሱስ አባት የሆነው የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ የመሐመድ አምላክም ይሆናል ማለት ነው። እርሱ በዚህ አምላክ ይመን አይመን ባላውቅም ማለት ነው።

ጽሑፌን ለማጠቃለል ያህል በዚህ ጽሑፍ አላህ የሚለው ስም ከእስልምና በፊት በአረብ ሀገራት ውስጥ አንድ ሁሉን የሚችል፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ፈጣሪ አምላክን ለማመልከት ይጠቀሙበት ስለ ነበር እና የቃሉ ሥርወ ግንድ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ኤሎሄም ጋር አንድ ስለሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠውን አምላክ አላህ ብሎ መጥራት በራሱ ምንም ችግር ስለምመስል ሰዎች ተለዋዋጭ ትርጓሜ እንዳላቸው ይናገራሉ። ነገር ግን የቃላት ትርጓሜ ምንጭ የቃላት ሥረወ ግንድ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡ የቃሉ አጠቃቀም እና ቃሉ በማህበረሱ አስተሳሰብ ውስጥ ከምን ጋረ እንደተቆራኘ እና ምን አንድምታ እንዳለው መመልከት ለቃሉ ትክክለኛ ትርጉም አዎንታዊ አስተዋጾ አለው። አላህ የሚለው ስም ለጣዖት ተስጥቷል የሚል ተቃዋሚ ካለ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው ኤሎሄም የሚለው ስምም ለጣዖት ተሰጥቶ ስለሚያውቅ ልዩነት የለውም እላለሁ። በሥረወ ግንድ ጥናት ብቻ ሁለቱ ስሞች በወል ስምነት መለኮትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውለዋል። ነገር ግን ቃላት ትክክለኛ አጠቃቀም እና ፍች ግን ሥረወ ግንድ ብቻ ሳይሆን ቃሉ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አሁን አጠቃቀም ትክክለኛውን ፍች ይሰጣል። ስለዚይህም በማህበረሰቡ ዘንድ አለህ እና እግዚአብሔር አቻ ትርጓሜ ስለሌላቸው እና ልዩነት እንዳላቸው ስለሚታመን አቻ፣ ተለዋጭ ትርጓሜ አድረገን መውሰድ አንችልም። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው አምላክ እና በቁራን የተገለጠው “አምላክ” አንድ ናቸው? ለሚለው ጥያቄ የእኔ ምላሽ አይደሉም የሚል ይሆናል። ይህ ግን በሁለቱ መካከል ምንም መመሳሰል አይኖረውም ማለት ግን አይደለም። ለዚህ ምላሽ መሠረት ያደረግሁት ሁለቱም ¹ይማኖቶች በምናብ፣ በሀሳብ እና በፍልስፍና አንድ ፈጣሪ እንዳለ በማመን እምነታቸውን በዚህ መሠረት ላይ የጣሉ ሳይሆኑ ሁለቱም ¹ይማኖቶች አምላካቸው እራሱን ገልጦበታል የሚሉት መጽሐፍት አሏቸው። እነዚህ መጽሐፍት የሚያመለክቱት አምላክ በአንድ አንድ ቦታዎች ላይ መመሳሰል ቢኖረውም አንድ አይነት ግን አይደሉም።

በመጨረሻ እውን “የኢየሱስ አባት እና የመሐመድ አምላክ” አንድ ናቸውን? ለሚለው ጥያቄ ምላሼ አይደሉም እና ናቸው እንደሆነ ገልጫለሁ። አይደሉም ያልኩበት ምክንያት የጥያቄአችን እሳቤ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው አምላክ እና በቁራን የተገለጠው “አምላክ” ላይ ስለሚሆን፤ ሁለቱ ደግሞ ምንም እንኳ የሚያመሳስላቸው ነገር መኖሩ የሚካድ ባይሆንም ልዩነት ስላላቸው፤ ምላሼ አይደሉም ሆኗል። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ሁሉን ፈጣሪ እና አምላክ በመሆኑ ምክንያት መሐመድም ከዘመናት በፊት ይኖር የነበረ ሰው ከመሆኑ የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ለእርሱም አምላክ ሊሆን ችሏል።

ስለዚህ ዛሬ በዚህ ጽሑፍ ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር ወንጌልን ሰዎች በሚረዱበት መንገድ ለማስተላለፍ እነርሱ በሚናገሩበት ቋንቋ፣ አስተሳሰብ፣ ባህል እና ወዘተ መናገሩ መልካም ሆኖ ሳለ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው አምላክን ከሌሎች አማልክት ጋር አንድ ማድረግ ግን አግባብነት የለውም ባይ ነኝ። አላህ የሚለውን ስም ወንጌልን ለምንነግራቸው ሰዎች አምላካችንን ለማመልከት መጠቀሙ አግባብነት ቢኖረውም በመጽሐፍ ቅዱሱ “አላህ” እና በቁራኑ “አላህ” መካከል ልዩነት እንዳለ ማሳየቱ ግን በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ማንኛውም የአውዳዊነት ግብ ሊሆን የሚገባው ወንጌልን ለሰዎች በሚረዱት መንገድ መልዕክቱን ሳይቀይጡ እና ሳይበርዙ ማስተላለፍ ነው። በባህላቸው ውስጥ የምናገኘውን ጠቃሚ እሴት ወንጌል ለማድረስ እንደ ጥርጊያ መንገድ ወይም ድልድይ ልንጠቀምበት እንችላለን እንዲሁም ልንጠቀምበት ይገባል። ነገር ግን ልዩነቱን አጉልተን ማሳየት ከተሳነን ወደ ቅይጣዊነት እንገባለን። ስለዚህ ጥንቃቄ እናድርግ እላለሁ። ለዛሬ በዚሁ አበቃሁ።

የግርጌ ማስታወሻ


[i] Timothy C. Tennent, Theology in the context of world historical Christianity, Grand Rapids, Zondervan, 2007.

[ii]ዚኒ ከማሁ

[iii] Survey of Islam, Allah, world of Islam [CD-Room] 2000

[iv] Allah, http://www.answers.com/library/ Wikipedia-cid-2091

[v]በቅንፍ ውስጥ ያለውን የጨመርኩት እኔ ነኝ

[vi] Timothy C. Tennent, Theology in the context of world historical Christianity, Grand Rapids, Zondervan, 2007. ገጽ 31

[vii] ዚኒ ከማሁ

[viii]Walton, John H.; Matthews, Victor H.; Chavalas, Mark W., The IVP Bible Background Commentary: Old Testament, (Downers Grove, IL: InterVarsity Press) c2000.

[ix] ISLAM, Microsoft ® Encarta ® 2008. © 1993-2007 Microsoft Corporation. All rights reserved.

[x] ዚኒ ከማሁ

[xi] Allah, http://www.answers.com/library/ Columbia Encyclopedia-cid-2091

[xii] ዚኒ ከማሁ

[xiii]ዚኒ ከማሁ

[xiv] ዚኒ ከማሁ

[xv] በዚህ ስፍራ የአንድ አምላክ አምልኮ የሚያመለክተው ሌሎች አማለክት መኖራቸውን የማይክደውን ነው።

[xvi]በቅንፍ ውስጥ ያለውን የጨመርኩት እኔ ነኝ

[xvii] Timothy C. Tennent, Theology in the context of world historical Christianity, Grand Rapids, Zondervan, 2007, 31

[xviii] Allah, International Standard Bible Encyclopedia, Copyright © 1915 The Howard-Severance Company. Database © 2007 WORDsearch Corp

[xix] ዚኒ ከማሁ 31

[xx] Allah, http://www.answers.com/library/ Mideast & N. Africa Encyclopedia -cid-2091

[xxi] ምንም እንኳ በዛሬው ጽሑፌ ባልዳስሰውም ስለ አንድነቱ ስናገሩም ሁለቱም ¹ይማኖቶች ልዩነት ልዩነተት አላቸው ብዬ አምናሉ።

[xxii] ትርጉም ከራሴ

[xxiii] ዚኒ ከማሁ 34

[xxiv] Timothy C. Tennent, Theology in the context of world historical Christianity, Grand Rapids, Zondervan, 2007. ገጽ41

[xxv] ዚኒ ከማሁ ገጽ 39

Leave a comment